አንዲት ትእዛዝ በልጁ በኢየሱስ ማመንና እርስ በርስ መዋደድ

ወዳጆች ሆይ፥ ልባችንስ ባይፈርድብን በእግዚአብሔር ዘንድ ድፍረት አለን፥ትእዛዙንም የምንጠብቅና በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን የምናደርግ ስለሆንን የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እናገኛለን። ትእዛዚቱም ይህች ናት፥ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናምን ዘንድ፥ ትእዛዝንም እንደ ሰጠን እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ።ትእዛዙንም የሚጠብቅ በእርሱ ይኖራል እርሱም ይኖርበታል፤ በዚህም በእኛ እንዲኖር ከሰጠን ከመንፈሱ እናውቃለን።

1.ዮሐ.3፡21-24

«ትእዛዚቱም ይህች ናት» ካለ በኋላ ናት፥ «በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናምን ዘንድ፥ ትእዛዝንም እንደ ሰጠን እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ።» ብሎ ሁለት ያደርጋቸዋል። ለመሆኑ ትእዛዚቱ አንዲት ናት ወይስ ሁለት? አንዲት ናት ይላል ነገር ግን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናምን ዘንድና ..እርስ በርሳችንም እንዋደድ ዘንድ በማለት ሁለት ያስመስላቸዋል? አዎ ዮሐንስ የመገለጥ ሐዋርያ ነው። የሚተርከው የተገለጠውን የተዳሰሰውን የተመለከትነውን ሕይወት ስለሆነ በመልእክቶቹ ዘንድ ተግባራዊ ያልሆነ የማንኖረው የማንመላለሰው እንዲሁ ለአእምሮአችን የምናውቀው አስተምህሮ የለም። ትምህርቱ የተገለጠና ተግባራዊ ነው። መልእክቱን ሲጀምር እንዲህ ብሎ ነበር የጀመረው።

« ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤ ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤» 1.ዮሐ.1፡1-2

ይህ ከመጀመሪያ የነበረው የሰማነው በአይኖቻችን ያየነው የተመለከትነው እጆቻችንም የዳሰሱት የሕይወት ቃል በኛም በምናምነው ዘንድ ሲተረክ ባህርዩ እንደዚሁ ነው። ይሰማል መሰማት ብቻ ሳይሆን ይታያል መታየት ብቻ ሳይሆን ይመለከታል መመልከት ብቻ ሳይሆን ይዳሰሳል። ይህ የተገለጠው የዘላለም ሕይወት የክርስቶስ ባህርይ ነው። ስለዚህ ዮሐንስ እርስ በርስ ስለመዋደድ ሲናገር ስለአስተምህሮ ሳይሆን ስለሚሰማ ስለሚታይ ስለሚዳሰስ ፍቅር መናገሩ ነው። በክርስቶስ መገለጥ የታየውና የተዳሰሰው ሕይወትና ፍቅር ዛሬም በቅዱሳኑ ይታያል ይዳሰሳል። ስለዚህ በክርስቶስ ስም ማመንና እርስ በርስ መዋደድ ሁለት ሳይሆን ሁለት በአንድ ወይም አንድ ትእዛዝ ነው። እርስ በርስ መዋደድ በክርስቶስ ከማመን ተለይቶ አይገኝም የለም እርስ በርስ መዋደድ ያለው በክርስቶስ ስም በማመን ውስጥ ነው። በክርስቶስ ማመን የሚታየው ደግሞ እርስ በርስ በመዋደድ ውስጥ ነው። እርስ በርስ መዋደድ በክርስቶስ ካመንን በኋላ በሂደት የምንጨምረው ሳይሆን በክርስቶስ የማመናችን ፊት ነው። ሰው በፊቱ እንደሚታይ በክርስቶስ ስም ማመናችን እርስ በርስ በመዋደዳችን ይታያል። ስለዚህ የሰጠን ትእዛዝ አንዲት ናት እርስዋም በልጁ በክርስቶስ እናምን ዘንድ ትእዛዝንም እንደሰጠን እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ። ልዩነታቸው እናትና ልጅ መሆናቸው ብቻ ነው። እርስ በርስ መዋደድ በክርስቶስ ስም የማመን ውጤት ነው። ነገር ግን የሚገኙት በአንድና በአንድ ጊዜ ነው። አንዱ ኖሮ ሌላው አለመኖር አይችልም። «በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ።» እንደሚለው ዓይነት ነው። ዮሐ.1፡1-2

ቃል የሆነው ወልድ ያልነበረበት ጊዜ አልነበረም። ሁልጊዜ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። በዘመኑ ፍጻሜ ግን ሰው ሆኖ ተገለጠ። እንደዚሁም ፍቅር በክርስቶስ ውስጥ ነበረ። ራሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ፍቅር ነው። ሕይወት የሆነው ክርስቶስ ከአብ ዘንድ ለኛ ሲገለጥ ፍቅር ተገለጠ። በስሙ አምነን ሕይወት ሲሆንልን እርስ በርስ መዋደድንም ተሞላን። ይህ እርስ በርስ መዋደድ በተቀበልነው ሕይወት ውስጥ ያለና በስሙ አምነን ሕይወት ካገኘንበት ቅጽበት ጀምሮ የምንኖረውና የምንመላለሰው ሕይወት ነው። ስለዚህ ሐዋርያው በክርስቶሰ ኢየሱስ ማመንና እርስ በርስ መዋደድን አንዲት ትእዛዝ አድርጎ አስቀመጣቸው። እንግዲህ በእምነታችሁ ውስጥ እርስ በርስ መዋደድን ካላገኛችሁ ያመናችሁት ክርስቶስን ሳይሆን ሌላ ነገር ነው ማለት ነው።

ሐዋርያው በመቀጠል እንደዚህ ይላል። «ትእዛዙንም የሚጠብቅ በእርሱ ይኖራል እርሱም ይኖርበታል፤» ልብ በሉ ትእዛዛቱንም አይደለም ያለው ትእዛዙንም ነው። የትኛውን ትእዛዝ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን እርስ በርሳችንም መዋደድ። ይህችን ትእዛዝ የሚጠብቅ በክርስቶስ ይኖራል ክርስቶስም በርሱ ይኖራል። ሕይወቱን በመቀበላችን የርሱ ኑሮ የኛ ኑሮ ስለሆነ አብሮ መኖር ተባለ። እርሱን በኛ እኛን በርሱ የሚያኖር ትእዛዝ ስለሆነ ችላ ሊባል አይገባም። በእርሱ መኖርን የወደደና ጌታችንና መድኃኒታችን አምላካችንም ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ እንዲኖር የወደደ አማኝ ሊቀበለውና ሊኖረው የተገባ መልካም ትእዛዝ። አሁንም ሐዋርያው ይቀጥላል። ከላይ እንዳልነው ሐዋርያው ግልጽና ተግባራዊ የሆነ ወንጌልን ነው የሚሰብከው እንጂ ግንዛቤን አይደለም የሚያስጨብጠው። ስለዚህ እኛ በጌታ መኖራችንና ጌታ በኛ መኖሩን እንዴት እንደምናረጋግጥ ደግሞ እንዲህ ያበስርናል። «በዚህም በእኛ እንዲኖር ከሰጠን ከመንፈሱ እናውቃለን።» በእኛ እንደሚኖር የምናውቅበት ውስጣዊው ማረጋገጫ ያለው ከሰጠን ከመንፈሱ ነው። ስለዚህ በክርስቶስ ያለው እምነታችን በውጭም በውስጥም ማረጋገጫ ያለ ህያው እምነት ነው። በውጭ ሰዎች ሁሉ የሚያዩት የእርስ በርስ ፍቅር በውስጥ ደግሞ ክርስቶስ የሰጠን መንፈሱ ነው። በውጭና በውስጥ መለበጥ ይሉአችኋል ይህ ነው። እግዚአብሔር ሙሴን ታቦቱን እንዴት መሥራት እንዳለበት ሲናገር «ከግራር እንጨትም ታቦትን ይሥሩ፤ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል ይሁን። በውስጥና በውጭም በጥሩ ወርቅ ለብጠው፤ በእርሱም ላይ በዙሪያው የወርቅ አክሊል አድርግለት።» ዘጸ.25፡10-11

ታቦቱ የተሠራው ከግራር እንጨት ቢሆንም በውስጥና በውጭ በወርቅ በመለበጡ ምክንያት ማንነቱ ጠፍቶአል። ሰዎች ሲያዩ የከበረና የሚያብረቀርቅ ወርቅ እንጂ እንጨትን አያዩም። ጥንካሬውም ወርቁ እንጂ ግራሩ አይደለም። ያ ታቦት ለአርባ ዓመታት በእስራኤል ፊት ሲጓዝ በግራሩ እንጨት ብርታት ሳይሆን በተለበጠበት ወርቅ ብርታት ነበር። የሚነቅዝ የሚሰበር የሚያረጅ ደካማ እንጨት በማይነቅዝ በማያረጅ በማይሰበር ብርቱ ወርቅ ተለብጦ በረታ። እንጨት በወርቅ ተሰውሮ የወርቅን ዘመን ኖረ። እግዚአብሔር እኛን በክርስቶስ ስም ያመነውን ሁሉ ያደረገው እንደዚሁ ነው። የመለኮቱ ባህርይ ተካፋዮች በማድረግ በውጭና በውስጥ በክርስቶስ ለበጠን። በውስጣችን የሚኖር መንፈሱን ሰጠን ። በውጭ ደግሞ የሚታይና የሚያበራ እርስ በርስ መዋደድን ሰጠን። ስለዚህ ውስጣችንም ውጫችንም በመለኮት ባህርይ በክርስቶስ ተለብጦአል። በስንፍናችን ዘመን እንዳልነው ውጬ (አንደበቴ) ነው እንጂ ውስጤ የዋህ ነው እንል ዘንድ አንደፍርም። በውጭ የማይታይ የማይዳሰስ ወንጌልን አናውጅም። ይህ ከአብ ዘንድ ለኛ የተገለጠው ሕይወት ባሕርይ አይደለም። በውስጣችን በመንፈሱ መለበጣችንን ሳንቀበልና የመንፈሱ ማደሪያ መሆናችንን ሳንረዳም የምኖረውን መልካም ኑሮ የምኖረው እኔ ነኝ ብለን በተወድሶ - ከንቱ አንናገርም። ይልቅስ በውጭም በውስጥም በተለበጥንበት ባሕርይ እንኖራለን። በክርስቶስ ኢየሱስ ስም ማመናችንንና ክርስቶስ በኛ እኛም በርሱ እንደምንኖር እርስ በርስ በመዋደዳችንና በምልልሳችን በሚፈነጥቀው ብርሃን እናሳያለን። ጌታችንም እንዳለው የእርሱ ደቀመዛሙርት መሆናችንን ዓለም በዚህ ያውቃል። ሌላኛው ሐዋርያ «በእነርሱም መካከል የሕይወትን ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ፥ ስለዚህም በከንቱ እንዳልሮጥሁ በከንቱም እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል።» ብሎ እንደተናገረው (ፊሊ.2፡16) በተራራ ላይ እንዳለችው ከተማ ብርሃናችንን በሰው ሁሉ ፊት እናበራለን። ይህንን ያዩ ሰዎች እኛ የተለየን ፍጡሮች እንደሆንን ወይም ለነጳውሎስ እንዳሉት ሰዎችን መስለን የወረድን ሌላ አማልክት ሲመስላቸው ደግሞ ልብሳችንን ቀደን (ክብራችንን ትተን) ይህ የምንኖረው ሕይወት በውስጣችን ያለውን መንፈስ የሰጠን ክርስቶስ እንደሆነ በመናገር በውስጥ መለበጣችንን እንመሰክራለን። ሐዋርያው ጴጥሮስ ከዮሐንስ ጋር ሆኖ ያንን ለብዙ ዘመናት ሽባ የነበረውን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሳና ተመላለስ ካለው በኋላ ውጤቱን ያዩ ሰዎች ትኩር ብለው ሲመለከቱአቸው የግራሩን እንጨት እንጂ የተለበጡበትን ወርቅ እንዳላዩ ስላስተዋለ እንዲህ አላቸው። « ጴጥሮስም አይቶ ለሕዝቡ እንዲህ ሲል መለሰ፦ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ በዚህ ስለ ምን ትደነቃላችሁ? ወይስ በገዛ ኃይላችን ወይስ እግዚአብሔርን በመፍራታችን ይህ ይመላለስ ዘንድ እንዳደረግነው ስለ ምን ትኵር ብላችሁ ታዩናላችሁ? የአብርሃምና የይስሐቅ የያዕቆብም አምላክ፥ የአባቶቻችን አምላክ፥ እናንተ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትንና ሊፈታው ቈርጦ ሳለ በጲላጦስ ፊት የካዳችሁትን ብላቴናውን ኢየሱስን አከበረው።» ሐዋ.3፡12-13

አዎ በውስጥም በውጭም በርሱ ተለብጠው ነበር። ስለዚህ በነርሱ የሚገለጠው ሁሉ የወርቁ እንጂ የነርሱ አልነበረም። ክርስቶስ በውስጣችን የሚኖር በኑሮአችንም የሚገለጥና የሚተረክ የመለኮት መልክ ነው።

ስለዚህም ከሐዋርያው ጋር እንዲህ ብለን እናውጃለን «እኔ ለእግዚአብሔር ሕያው ሆኜ እኖር ዘንድ በሕግ በኩል ለሕግ ሞቼ ነበርና። ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው።» ገላ.2፡19-20።

በመንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ያደረና በኑሮአችን በየዕለቱ እርስ በርስ በመዋደድ የሚገለጠው ክርስቶስ ኢየሱስ ከዘላለም እስከ ዘላለም የተመሰገነ ይሁን።

«ትእዛዚቱም ይህች ናት፥ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናምን ዘንድ፥ ትእዛዝንም እንደ ሰጠን እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ።» 1.ዮሐ.3፡23

Created By
ጸጋ ብርሃን
Appreciate

Made with Adobe Slate

Make your words and images move.

Get Slate

Report Abuse

If you feel that this video content violates the Adobe Terms of Use, you may report this content by filling out this quick form.

To report a Copyright Violation, please follow Section 17 in the Terms of Use.